መግቢያ
ኢትዮ አግሪ -ሴፍት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በሚድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቡድን ስር የሚገኝና በግብርናና አግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማራ የግል ኩባንያ ሲሆን በውጤታማ የልማት ጉዞው ስኬታማ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡ በኢትየጵያ ከሚገኙ ሰፋፊ የእርሻ ልማቶች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ መሆኑንም አስመስክሯል፡፡ በ1990 ዓ.ም. ጥር ወር የገማድሮ ቡና ልማትን በመረከብ ሥራውን በ30 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የጀመረው ኩባንያችን በአሁኑ ወቅት ካፒታሉን ከ686 ሚሊዮን ብር በላይ አሳድጓል፡፡ የልማቶቹንም ቁጥር በመጨመር የዘጠኝ ግዙፍ እርሻ ልማቶችና የአንድ የሻይ ምርት ማዘጋጃና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ባለቤት ሆኗል፡፡

በኢትዮ አግሪ -ሴፍት ስር የሚገኙ የእርሻ ልማቶች
የእርሻ ልማቱ ስም ጠቅላላ የቆዳ ስፋት /በሄክታር/ በቋሚ ተክል/ዓመታዊ ሰብል የተሸፈነ መሬት (በሄክታር)
ገማድሮ ቡና ልማት 2,217 1,153
ዱየና ቡና ልማት ፕሮጀክት 1,573 934.3
ውሽውሽ ሻይ ልማት 4,263 1,253
ጉማሮ ሻይ ልማት 2,603 867
ብር እርሻ ልማት 8,851 7,539
አየሁ እርሻ ልማት 6,688 4,975
የሆለታ አበባ ልማት 28 14.46
ባህር ዳር አበባና ፍራፍሬ ልማት 50 50
በሃ ላንድ አግሮ ኢንዱስትሪ 288.87 287
ድምር 26,561 17,028

የኩባንያው አመሠራረት፣ አደረጃጀትና የሰው ኃይል
ኢትዮ አግሪ-ሴፍት ኃ.የተ.የግል ማኀበር ጥር 1990 ዓ.ም. በብር 30,000,000 ተከፋይ ካፒታል ተመስርቶ የገማድሮ ቡና ልማትን በማደራጀት ስራውን የጀመረ ሲሆን በቀጣይም ኩባንያው ውሽውሽና ጉማሮ ሻይ ልማቶችን፣ የሻይ ምርት ማዘጋጃና ማቀነባበሪያ ፋብሪካን፣ የብርና የአየሁ እርሻ ልማቶችን ከመንግሥት በመግዛት እንዲሁም ሆለታ የአበባ እርሻ፣ የዱየና ቡና ፕሮጀክት እና ባሕርዳር የአበባና አትክልት ፕሮጀክት በማቋቋም በእርሻና በንግድ ስራ የተሰማራ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቡድን እህት ኩባንያ ነው፡፡ በቅርቡም የበሃ ላንድ አግሮ ኢንዱስትሪን በመግዛት የቡና እርሻ ልማቶቹን ወደ አራት ከፍ ከማድረጉም በተጨማሪ በጋምቤላ ክልል በአበቦ ወረዳ የአበቦ እርሻ ልማትን ተረክቦ ሩዝ ያለማ ይገኛል፡፡ :: በሰው ኃይል ረገድ ኩባንያው በዋና መሥሪያ ቤት፣ በሚያስተዳድራቸው ዘጠኝ የእርሻ ልማቶችና አንድ የሻይ ማዘጋጃና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ከ18,743 በላይ ለሚሆኑ ቋሚ፣ ኮንትራትና ጊዜያዊ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሮአል፡፡
የኩባንያው ዓላማዎች
ቡና፣ ሻይና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ሰብሎች አምርቶና አቀነባብሮ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ
ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ
ዘላቂ ለሆነ የምርት ጥራት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት፣
የአካባቢን ስነምህዳር በጠበቀና ባገናዘበ መልኩ የልማት ሥራዎችን ማካሄድ፣
የኩባያው ሠራተኞች ዕውቀታቸውን እንዲያዳብሩ በየወቅቱ የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና መስጠት፣
የሠራተኞችን ደህንነትና ምቾት በየጊዜው ማሻሻል፣
ለኢትዮጵያውያን ወገኖች የሥራ ዕድል መፍጠር፣
የኩባንያው ዋና ዋና ምርቶች
ቡና
ኩባንያው ከሚያመርታቸው የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙ ምርቶች ውስጥ አንዱና ዋናው ቡና ሲሆን ኩባንያው የቡና ልማት የጀመረውም በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ በሸካ ዞን በአንደራቻ ወረዳ ልዩ ስሙ ገማድሮ በሚባል አካባቢ ነው፡፡ በዚሁ ክልል ተጨማሪ ሁለት የቡና ልማቶች ሲኖሩት ከገማድሮ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ 1573 ሄክታር መሬት ተረክቦ የዱየና ቡና ፕሮጀክትን እንዲሁም ሶስተኛው የቡና ልማት በሃ ላንድ አግሮ ኢንዱስትሪ በከፋ ዞን፣ ዲቻ ወረዳ ባሃ ቀበሌ በ288.87 ሄክታር መሬት ላይ የቡና ልማት እያስፋፋ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩልም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአዊ ዞን ውስጥ በአየሁ እርሻ ልማት ውስት 300 ሄክታር የቡና ልማት እያስፋፋ ይገኛል፡፡
1. የገማድሮ ቡና ልማት ይዞታ 2217 ሄክታር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 1153 ሄክታሩ በቡና ተክል የተሸፈነ ነው፡፡ የቡናው ልማቱ በሚገኝበት አካባቢ ስም ገማድሮ ቡና በሚል ተሰይሟል፡፡
2. የዱየና ቡና ፕሮጀክት ይዞታ 1573 ሄክታር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 934 ሄክታሩ በቡና ተክል የተሸፈነ ነው፡፡
3. በሃ ላንድ አግሮ ኢንዱስትሪ ይዞታ 288.87 ሄክታር ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 288 ሄክታሩ በቡና ተክል የተሸፈነ ነው፡፡
4. የአየሁ ቡና ይዞታ 300 ሄክታር ሲሆን በዝናብና በመስኖ በመታገዝ እያመረተ ያለውን ቡና ደረጃ በደረጃ እስከ 1000 ሄክታር ለማድረስ ከፍተኛ ስራ በመስራት ላይ ነው፡፡
የገማድሮ ቡና በጥራቱና በጣዕሙ
. የUTZ KAPEH ፣ Rainforest Alliance እና BSC OKO-Garanti GmbH አለም አቀፍ ተቋማት የምስክር ወረቀት አግኝቷል፡፡
. የገማድሮ ቡና በጥራቱ ስታርባክስ ከተባለው ግዙፍ የአሜሪካ የቡና ኩባንያ እውቅናና ሁለት ጊዜ ሽልማት አግኝቷል፡፡
. በተጨማሪም የአየሁ ቡና ከRainforest Alliance የምስክር ወረቀት አግኝቷል፡፡
ሻይ
ውሽውሽና ጉማሮ ሻይ ልማቶች
ጉማሮ ሻይ ልማት በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በኢሉ አባቦራ ዞን በአሌ ወረዳ ከአዲስ አበባ 630 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ 867 ሄክታር የሚሸፍን የሻይ ተክል አለው፡፡ በዓመት በአማካይ ከ26,010 ኩንታል በላይ ሻይ ቅጠል ያመርታል፡፡
ውሽውሽ ሻይ ልማት በደቡብ ብ/ብ/ሕ/ክልላዊ መንግስት በከፋ ዞን በጊምቦ ወረዳ ከአዲስ አበባ 460 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ልማቱ 1,253 ሄክታር ሻይ ተክል የሚያስተዳድር ሲሆን በዓመት በአማካይ ከ40,000 ኩንታል በላይ ሻይ ቅጠል ያመርታል፡፡
ውሽውሽና ጉማሮ ከተፈጥሮ ሃብት አጠባበቅ አኳያ
የሻይ ልማቶቻችን ለተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና እንክብካቤ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ በወንዞች፣ በሸለቆዎችና በተዳፋት ቦታዎች ዳርቻ የሀገር በቀል የዛፍ ዝርያዎችና ሌሎች ዕፅዋቶች እንዲጠበቁ በማድረግ ለአካባቢው አየር ሚዛን/ ስነ ምሕዳር መጠበቅ አስተዋፅኦ በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ልማቶቹ የሚገኙበት አካባቢ ከፍተኛ የዝናብ መጠን የሚመዘገብበት በመሆኑ አፈር በጎርፍና በዝናብ እንዳይታጠብ ከፍተኛ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
ለልማት በማይውሉ ቦታዎችና በተዳፋት አካባቢዎች ላይ የሀገር በቀል፣ የውጭ ሀገር የዛፍ ዝርያዎች እንዲለሙ እየተደረገ ነው፡፡ በሁለቱም ልማቶች ከሻይ ተክል ውጭ ከ30% በላይ የሚሆነው መሬት በዕፅዋት ተሸፍኖ ይገኛል፡፡ ይህም የሚያሳየው ለተፈጥሮ ሃብት እንክብካቤ የተሰጠው ትኩረት ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ በልማቶቹ የሚከናወኑት የልማት ስራዎች ዘለቄታዊ ሊሆኑ የሚችሉት የተፈጥሮ ሃብትን በማይጎዳ መልኩ ሲከናወኑ መሆኑ ስለታመነበት በዚህ ረገድ እስካሁን የተከናወኑት ስራዎች ውጤታማ ናቸው፡፡ ለዚሀም ሁለቱም ልማቶች ከRainforest Alliance ከተባለ ዓለም አቀፍ ተቋም ከአካባቢ ጋር የተጣጣመ ተግባራት እንደሚያከናውኑ ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት አግኝተዋል፡፡
በገበያ ላይ የሚገኙ የታሸጉ የሻይ ምርቶች
ኢትዮ አግሪ-ሴፍት ኃ/የተ/የግል ማኅበር የሻይ ምርት ማዘጋጃና ማቀነባበሪያ ፋብሪካን ሲረከብ በተለያየ መንገድ አሽጎ ገበያ ላይ የሚያቀርበው ምርት ጥቁር ሻይ (Black Tea) ብቻ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ከከሞሜላ አንስቶ አረንጓዴ ሻይ፣ የተቀመሙ የተለያዩ የሻይ ዓይነቶች ከፍተኛ ተቀባይነት በማግኘት ገበያ ላይ ውለዋል፡፡
በሻይ ልማቶቹ የሚመረተው የሻይ ምርት አዲስ አበባ ውስጥ ባለው የሻይ ምርት ማዘጋጃና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ እየተዘጋጀ፣ ጥራቱ እየተረጋገጠ፣ ደረጃ እየወጣለትና እየታሸገ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እየቀረበ ነው፡፡ ፋብሪካው ውሽውሽ ሻይ፣ ጉማሮ ሻይ፣ አዲስ ሻይ፣ ዝንጅብል ሻይ፣ ጦስኝ ሻይ፣ ቀረፋ ሻይ፣ ከርከዴ ሻይና ካሞሜላ ሻይ አዘጋጅቶና አሽጎ ለሀገር ውስጥ ገበያ ያከፋፍላል፡፡
ልዩ ልዩ ሰብሎች
የጎጃም እርሻዎች በ1993 መጨረሻ ላይ በሽያጭ ከመንግስት ወደ ኢትዮ አግሪ-ሴፍት ተዛውሯል፡፡ እነሱም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ውስጥ ብርና አየሁ የተባሉ የሰብል እርሻዎች ናቸው:: የብር እርሻ የመሬት ስፋት 8,851 ሄክታር እንዲሁም አየሁ እርሻ 6,688 ሄክታር የመሬት ሽፋን አላቸው፡፡ ኩባንያው ለብርና አየሁ እርሻ ልማቶች አስፈላጊ የእርሻ መሳሪያዎች ያሟላላቸው በመሆኑ የልማቶች የስራ እንቅስቃሴ ማለትም ከመሬት ዝግጅት ጀምሮ እስከ ሰብል ስብሳቦ ድረስ በአብዛኛው ሜካናይዝድ በሆነ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
ስለዚህ በእርሻ ልማቶቹ ለአካባቢ ስነምህዳር መጠበቂያነት በተለያዩ አገር በቀልና የውጭ ዝርያ ባላቸው ዛፎችና በተለያየ መሠረተ ልማቶች ከተያዘው መሬት ውጭ ቀሪው ይዞታዎች ሙሉ ለሙሉ የለማ ከመሆኑም በላይ የትኩረት አቅጣጫውን ይበልጥ በማጠናከር በ455 ሄክታር መሬት ላይ በሴንተር ፒቮት ኢሪጌሽን በዓመት ሁለት ጊዜ ለማምረት የሚያስችል የመስኖ ስራ እያስፋፋ ይገኛል፡፡ በተጨማሪ በሁለቱም እርሻዎች በመስኖ በመታገዝ አትክልትና ፍራፍሬ፣ መዓዛማ ተክሎችና ለመድኃኒትነት የሚያገለግሉ ተክሎችን በማምረት ለአካባቢው፣ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡
በእነዚህ እርሻዎች በዋናነት በቆሎ፣ አኩሪ አተር፣ በርበሬ፣ ሽምብራ፣ ቦለቄ ወዘተ…. ይመረታል፡፡ እርሻዎቹ በተጠቀሱት ሰብሎች ላይ ቢያተኩርም የሰብል ስብጥር ለውጥ ደረጃ በደረጃ እየተካሄደ ነው፡፡
በአየሁ እርሻ ልማት ድቃይ የተመሰከረለትና መስራች የበቆሎ ዘር ለአርሶ አደሮችና ለዘር አባዢዎች እያመረተ ያከፋፍላል፡፡ በተጨማሪ በዚሁ እርሻ ልማት በዝናብና በመስኖ እገዛ ካለማው 300 ሄክታር የቡና ተክል በተጨማሪ ደረጃ በደረጃ እስከ 1000 ሄክታር ለማድረስ ከፍተኛ ስራ በመስራት ላይ ነው፡፡
ኩባንያው በሰብል ማምረት ስራ ላይ ብቻ ሳይወሰን ምርቱን ወደ አግሮ ኢንዱስትሪ ለመቀየርና በተረፈ ምርቱም የከብት ማደለብ ስራን በዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
አበባ
ኢትዮ አግሪ-ሴፍት የአበባ እርሻን የጀመረው በ1997 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአምቦ መስመር ሆለታ አካባቢ ባገኘው 28 ሄክታር የእርሻ መሬት ላይ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት 14.3 በሄክታር በዘመናዊ ግሪን ሃውስ በተከለለ መሬት የተለያዩ አይነት የፅጌረዳ ዝርያዎች ተሸፍኗል፡፡ የእርሻው ስም ኢትዮ አግሪ-ፍላወርስ ይባላል፡፡
ሆለታ አግሪ ፍላወርስ አስራ አንድ (11) ዓይነት የደጋ የፅጌረዳ ዓይነቶች የሚያለማ ሲሆን በዓመት እስከ 12 ሚሊየን የፅጌረዳ ዘንጎች ለማምረት አቅም አለው፡፡
እነዚህ የፅጌረዳ ዘንጎች በሳምነት አራት ጊዜ ወደ ኔዘርላንድስ በጨረታ እና በቀጥታ ሽያጭ ወደ ሳውዲ አረቢያ፣ ጣሊያን፣ ኦማን፣ ወዘተ…. እያቀረበ ይገኛል፡፡ ኢትዮ አግሪ ፍላወርስ የሚመረተው የደጋ ፅጌረዳ አበባ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተቀባይነት እንዳለው የሚያረጋግጥ ሰርትፊኬት አግኝቷል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ኩባንያው በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች የኢንቨስትመንት ስራውን ለማስፋፋት ባለው ዕቅድ መሠረት ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባህርዳር ከተማ በባህርዳር ዙሪያ በሮቢት ባታ ቀበሌ ተጨማሪ በተረከበው 50 ሄክታር መሬት የአበባ ልማት ስራ እያከናወነ ሲሆን የማምረት ሂደቱም በአሁኑ ወቀት ተጀምሮ የተከላ ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
በአጠቃላይ ከላይ በተጠቀሱ እርሻ ልማቶች ለበርካታ የሀገራችን ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድሎች የተፈጠሩ ከመሆኑም በላይ የኩባንያው ምርቶች ከሀገር ውስጥ ገበያ አልፈው ወደ ውጭ ስለሚላኩ ለሀገራችን የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት በኩል ኩባንያው የበኩሉን ድርሻ በስፋት እየተወጣ ይገኛል፡፡